12/03/2026
"በክልሉ ጋሞ ዞን በተለያዩ አከባቢዎች በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ እስከ አሁን የ70 ሰዎች ህይወት አልፏል"፦ የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት
ዎላይታ ሶዶ፣መጋቢት 3/2018 (ዎጌታ ኤፍ ኤም 96.6)
በአደጋው ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ጊዜያዊ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር በዘላቂነት ለማቋቋም በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ተመላክቷል
የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይለማሪያም ተስፋዬ አደጋውን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የጋዜጣዊ መግለጫ ዋና ዓላማ በአደጋው የደረሰውን ጉዳት ለማሳወቅና የሠብዓዊ ድጋፍ ለማሰባሰብ ያለመ መሆኑም በመግለጫው ተጠቁሟል።
የአገልግሎቱ ኃላፊ እንደገለፁት መጋቢት 01/2018 ዓ.ም በጋሞ የተለያዩ አከባቢዎች በጣለው ከባድ ዝናብ በ4 ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።
አደጋው 3 ሺህ 480 የቤተሰብ ዓባላት ያሉዋቸው 575 አባወራና እማወራዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ማፈናቀሉንም የአገልግሎቱ ኃላፊ አቶ ኃይለማሪያም አብራርተዋል።
በዞኑ በተከሰተው አደጋ 190 የመኖሪያ ቤቶች የወደሙ ሲሆን እስከ ቀኑ 8 ሰዓት ድረስ የ70 ሰዎች አስከሬን መገኘቱንም ጠቁመዋል።
በተያያዘም በአርባ ምንጭ ከተማ የኩልፎ ወንዝ በመሙላት ተፈጥሮአዊ አቅጣጫውን ለቆ በመሄድ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ 31 በተለያዩ ደረጃ የሚገኙ ማህበራት፣ 2 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችና 1 የግብረ ሰናይ ድርጅት ንብረት ውድሟል።
የክልሉ መንግስት በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ እንዲሁም የጤና አገልግሎት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አቶ ኃይለማሪያም ገልፀዋል።
በቀጣይ 10 ቀናት ዝናቡ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሜትሮሎጂ ትንበያ ይገልፃል ያሉት የአገልግሎቱ ኃላፊ በስጋት አከባቢዎች የሚገኙ ዜጎች አከባቢውን እንዲለቁ የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
አደጋውን አስመልክቶ የአይነት ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ተቋማትና ግለሰቦች አርባምንጭ ከተማ በመምጣት የጋሞ ዞን አስተዳደርን ሊያገኙ እንደሚገባ የገለፁት አቶ ኃይለማርያም የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ 1000321312865 የጋሞ ዞን አደጋ ስጋት ጽ/ቤት በሚል የሂሳብ ቁጥር እንዲያስገቡ አሳስበዋል።
ህብረተሰቡ በአደጋው ህይወታቸው ያጡ ወገኖችን ፎቶና የቪዲዮ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ከመልቀቅ ሊቆጠብ ይገባል ያሉት አቶ ኃይለማሪያም ትክክለኛ መረጃዎችን ብቻ ሊከታተል እንደሚገባም አሳስበዋል።
በአደጋው ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ ጉዳት መድረሱን ያወሱት ኃላፊው በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚገኙ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ አደጋ ስጋት ምክር ቤት በጋሞ ዞን እና አርባ ምንጭ ከተማ በተከሰተ የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋ ፈጣን ምላሽ መስጠት በሚቻልበት ዙሪያ በመምከር የተለያዩ አቅጣጫዎች ማስቀመጡንም አቶኃይለማሪያም ተስፋዬ በሰጡት ጋዜጣዊ በመግለጫ አስታውቀዋል።
በማንኛዉም ሰዓት ጥቆማና አሰተያየት ለመስጠት
የስልክ መስመራችን ክፍት ናቸው ይደውሉ
ስልክ - 0461809999
0461801609
0964647777
በተጨማሪም ይህንን የፌስቡክ ገጻችንን https://www.facebook.com/wogeta?mibextid=ZbWKwL Follow, Share, Like, በማድረግ ቤተሰብ ይሁኑ።
ለቀጥታ ስርጭት linkኩን ይጫኑ https://zeno.fm/radio/wogeta-fm-96-6-lw1u
ትጋትና ታማኝነት ለብልፅግና!