01/03/2025
ምስኪን ዘለንስኪ 2
የምሥራቅ አውሮፖዊቷ ዩክሬን ፕረዝደንት፤ የ47 ዓመቱ ጎልማሳ ቮሎድሚር ኡልዲሚሮቪች ዘለንስኪ የዛሬ 3 ዓመት ዘለው ከሩስያ ጋር ጦር ውስጥ የተዶሉት አይዞህ ባያቸውን ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካንን ተማምነው ነው። አሜሪካም አላሳፈረቻቸውም። በቃሏ መሰረት ዩክሬንን በገንዘብ፣ በመሣሪያ፣ በሞራል ስትደግፍ ከመቆየት አልፋ የአውሮፓ ሀገራት ከዩክሬን ጎን እንዲቆሙ ብዙ ለፍታለች።
በግልፅ ዩክሬንን ወግናም በሩስያ ላይ በዋንኛነት የኢኮኖሚ፣ የፋይናንስ ማዕቀብ በመጣል ከባድ ፍጥጫ ውስጥ እስከመግባት ደርሳለች።
ዕድሜ ለትራምፕ ሩስያ ዛሬ ያ ጫናዋ ተረስቶ በአሜሪካ የምትወደስ ሀገር ለመኾን በቅታለች።
በተቃራኒው ተጧሪዋ ዩክሬን ዓይንሽ ላፈር መባሏ ሳያንስ በግልፅ አሜሪካ ለጦርነቱ አውጥተዋለች የተባለው 500 ቢልየን ዶላር በዓይነት እንድትከፍል ተጠይቃለች።
ይኸ ለእነዘለንስኪ ከጦርነቱ የከበደ ዲፕሎማሲያዊ ውድቀትን ይዞ መጥቷል። ከምንም በላይ ባልገቡት ኮንትራት "ላወጣነው ገንዘብ የተፈጥሮ ሐብታችሁን (ማዕድን) ስጡን" የሚለው እጅ ጥምዘዛ የሚፋጅ እሳት ሆኖባቸዋል።
የዩክሬኑ ፕረዝደንት በዚህ ኹሉ ቀውስ ውስጥ ኾነው፣ ሳይወዱ በግድ የተፈጥሮ ሐብታቸው አሜሪካ መጠቀም እንድትችል የሚፈቅደውን ፊርማ ለማኖር 5 ሺ 300 ማይል ወይም ከ10 ሰዓት በላይ የአየር በረራ ተጉዘው ኋይት ሐወስ ተገኙ። ለፕሮቶኮል ብዙም ሳይጨነቁ ቀለል ባለ አለባበስ ትራምኘ ቢሮ የተገኙት ዘለንስኪ ከትራምፕና ምክትላቸው የገጠማቸው በኃይለቃል የታጀበ ሙግት ሰምቶ ማለፍ ተስኗቸው የመጡበትን ጉዳይ ሳይፈፅሙ ለመመለስ ተገደዋል።
ዘለንስኪ ዛሬ አሜሪካንን ተማምነው የጀመሩት ኹሉ ውሀ በልቶታል። "ጦርነት ቆስቋሽ" ከመባል አልፈው "አምባገነን" ተብለው በአደባባይ ተዘልፈዋል። በትላንቱ ውይይትም "በሚልየኖች ሕይወት የምትቆምር" ተብለዋል። የኔቶ አባል ሀገር ለመኾን የነበራቸው ተስፋና ሕልም "እንዳታስበው" በሚለው የትራምፕ ቃል እስከወዲያኛው ተቆልፏል። እኚህ ሰው ታዲያ በአሜሪካ ነገረ ድርጊት ቢበሳጩና ስሜታዊ ኾነውም ቢታዩ ይፈረድባቸዋልን?
ምስኪን ዘለንስኪ?!😘
👉