14/11/2025
☞አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ያደረገው ተአምር ይህ ነው፡፡
☞ብዙ መድኃኒት የሚያደርግ አምልኮ ባዕድ የሚወድ፤ ብዙጊዜ ዝሙት
የሚፈጽም አንድ ኅጢአተኛ ሰው ነበር፡፡
☞አንድ ቀንም ንዑድ ክብር የሚሆን የአባታችን ገብረ መንፈስ ቅዱስ የገድሉ
መጽሐፍ በሚነበብበት መጋቢት 5 ቀን ሔደ፡፡
☞ጌታ ለሰዎች የምሕረት ቃል ኪዳን እንደገባለት የቃልኪዳኑ መጽሐፍ በእዝነ
ልቡናው አደመጠ(ሰማ) በልቡም ያ ኃጢአተኛ መነኩሴም በሕሊናው እኔ
መታሰቢያውን አደርጋለሁ፤በጸሎቱም እታመናለሁ ብሎ አሰበና የአባታችን
የገድሉን መጽሐፍ ተሳልሞ ወጣ፡፡
☞ከዚያም ተነሥቶ፤ ሲሔድም በመንገድ ወንቤዴዎች አገኙት፤በታላቅ ዱላም
ደብድበው ልብሱን ገፈፋት፤በደም እየተጠመቀም ወደ ቤቱ ገባ፡፡
☞በዚያች ሌሊትም በእግዚአብሔር ፈቃድ ሞተ፤መላእክተ ጽልመትም መጥተው
ያችን ነፍስ ከበቡአት ወሰደውም ወደ እግዚአብሔር ፊት አደረሷት፡፡
☞እግዚአብሔርም መላእክተ ጽልመት ሒዱ ይህችን ነፍስ ወደ ሲኦል
ውስዷት፤በክፋ ሽታዋ ሰማይን (መካነ ነፍሳትን) አታርክስ ወደ ሲኦልም አስገቧት
አለ፡፡
☞ያን ጊዜም መላእክተ ጽልመት ያችን ነፍስ ወደ ሲኦል ወሰዷት አባታችን ገብረ
መንፈስ ይህን ነገር በመንፈስ ቅዱስ ዐወቀ፤ ከብርሃን ማደሪያው ተነሥቶ
በእግዚአብሔር ፊት ሰገደና አቤቱ፤ ሰማይ ምድር በቃል ኪዳንህ ጸንተው
ይኖራሉ፤ቃልህ ለምን ይታበላል፤ አቤቱ ከአንደበትህ የወጣው የሰጠኸኝን ቃል
ኪዳን አሰብ አለው፡፡
☞ጌታም መልሶ ወዳጄ ምን ዋሽውህ አለው፤ አባታችንም ክፋዎች መላእክተ
ጽልመት የወሰዱት ይህ ሰው በጸሎቴ ተማፅኖ እርሱ መታሰቢያዬን አደርጋለሁ
ብሎ ነበር ሞቱም በዕረፍቴ ቀን ሆኗል አለው፡፡
☞ያን ጊዜም የዚያ ሰው ኅጢአቱ ብዙ ስለሆነ ጌታ ዝም አለ፤ አባታችንም፤
በዙፋኑ ሰገደና ይህን ሰው መማር ካልወደድክ ከእርሱ ጋር ጨምረኝ አለው፡፡
☞ያን ጊዜም እግዚአብሔር መልአኩ ቅዱስ ሚካኤልን ፈጥነህ ሒድና ወደ
ሲኦል ሳይጨምሯት አምጣት አለው፤
☞ቅዱስ ሚካኤል ሄዶ በእሳት ባሕር ዳር አገኛትና መልሶ ወደ እግዚአብሔር
ፊት አደረሳት፡፡
☞እግዚአብሔር ያችን ነፍስ ለወዳጄ ለገብረ መንፈስ ቅዱስ ምን ረድርገሽለታል
አላት፡፡
☞ያች ነፍስም የገድሉን መጽሐፍ በሰማሁ ጊዜ ልቡናዬ ደስ አሰኘኝ፤ በልቤም
መታሰቢያውን ላደርግ አሰብኩ፤ ልቡናዬም በፍቅሩ ተቃጠለ፤ ገድሉንም ተሳልሜ
ሔድኩ፤ በዚያች ቀንም ሽፍቶች ገደሉኝ፤ ወደ አንተም ደረስኩኝ አለችው፡፡
☞እግዚአብሔርም ያችን ነፍስ እርሱን በመውደድ ልብሽ ከተቃጠለ፤በጸሎቱም
ከተማፀንሽ እኔም ኅጢአትሽን ይቅር ብየሻለሁ፣ በደልሽንም ደምስሼልሻለሁ
አላት፡፡
☞ይህንም ተናግሮ ወደምእመናን ጻድቃን መኖሪያ እንዲወስዷት አዘዘ፤ ፈጥነው
ወሰዷት፤ አባታችን አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስም ተደሰተ ፊቱ በራ፡፡
☞የጻድቁ አባታችን የአቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ጸሎቱና በረከቱ ከሁላችን ጋር
ይሁን፡፡
☞(ገድ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ)
☞ሲራክ ተክለጻዲቅ የተዋህዶ ልጅ